Contac: Sodoweredasitoffice@gmail.com
History
የጢያ መካነ ቅርስና አካባቢው ታሪክ
በርካታ የአርኬዎሎጂና የታሪክ ባለሙያዎች እንሚስማሙበት ከሆነ የጢያ ትክል ድንጋዮች ሶዶ ተብሎ በሚጠራው የመካከለኛ ኢትዮጵያ የሜጋሊቲክ ባህላዊ ትውፊት አካል ነው፡፡ ሶዶ ተብሎ ይጠራ የነበረው ክልል ከአዲስ አበባ በስተደቡብ ምዕራብ 45 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ከሚገኘው የአዋሽ ወንዝ አንስቶ እስከ 125 ኪ.ሜ ርቀት ያለውን ስፍራ ሁሉ ይሸፍን እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎችም ሆኑ አውሮፓውያን አገር አሳሾች ያትታሉ፡፡ የያኔው ሶዶ የዛሬዎቹ ሌመን፣ጢያና ቡኢን ከተሞች በሞላ ያካተተ ነው፡፡
ይሁን እንጅ አውሮጳውያን አገር አሳሾችና ዲፕሎማቶች ሶዶ የሚለውን ስያሜ በቦታ ስምነት መጥቀስ የጀመሩበት ዘመን ከ19ኛው ክፍለ ዘመን የዘለለ አይደለም ፡፡ ነገር ግን በአካባቢው ዛሬ በብዛት ሰፍረው የሚኖሩት ጉራጌዎች ወደ አካባቢው መጥተው የሰፈሩት በ14ኛው ክፍለ ዘመን እንደሆነ ያምናሉ፡፡ አንዳንድ የታሪክ መዛግብትም ይህንኑ ይናገራሉ(ለምሳሌ አለቃ ታዬ፣1964፣ ሃንቲንግፎርድ 1965)፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ሶዶ የሚለው ስም በቦታ ስምነት የጠቀሱት አሴንበርግና ክራፈ የተባሉ አውሮፓውያን ናቸው፡፡ በ1839 ዓ.ም አካባቢውን የጎበኙት እነዚህ አውሮፓውያን ሶዶ በደቡብ ሸዋ የምትገኝ ቦታ መሆኗን በመጥቀስ ለሸዋ ንጉስ ግብር ትገብር እንደነበር አትተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሶዶ የአንድ የኦሮሞ ነገድ መጠሪያ መሆኑን አስምረውበታል፡፡
ሌላው አውሮፓዊ ሮቺ ዴ ሊቲኮርት በበኩሉ የሸዋ ንጉስ ሳህለ ሥላሴ ከሶዶ ኦሮሞዎች ጋር በ1846 ዓ.ም መዋጋታቸውን በመጥቀስ በዚሁ ጦርነት የሸዋ ንጉስ በርካታ የቀንድ ከብት መማረካቸውን አትቷል፡፡ ይህም ሶዶ በርካታ የቀንድ ከብት የነበረበትና ለቀንድ ከብትና ለእርሻ ተስማሚ የነበረ ስፍራ እንደነበር ይጠቁማል፡፡ በሁለቱ ኃይላት መካከል ጦርነቱ በትክክል በሶዶ ስለማሄዱም ቴዎፈሌ የተባለ ጎብኝም ጠቁሞ አልፏል፡፡
የሸዋ ነገስታት መዲና አንኮበርን እ.ኤ.አ በ1844 የጎበኘው ዋሊስ ሐሪስ ለንበብ በበቃው መፅሐፍ ሶዶን ከአዋሽ ወንዝ በስተደቡብ የምትገኝ ሥፍራ አድርጎ ጠቅሶታል፡፡ አንቶኒዮ ዲ አባዲ በበኩሉ “ GEOGRAPHIC DE ETHIOPIE “ በሚል ርዕስ ባለው መፅሐፍ ሶዶ የኦሮሞ ነገድ የሆኑት የቱለማና ዳቻ ልጅ ነው ሲል ይገልፀዋል፡፡ ዛሬ ግን ሶዶ የሚለው ስያሜ ቀጥተኛ ትርጉም በኦሮሞ ቋንቋ ውስጥ ማግኘት አይቻልም፡፡ (አንፍሬ ፣1982) ፡፡ በተመሳሳይ የቃሉ ፍቺም በጉራጊኛ ቋንቋ ውስጥም የለም፡፡ ይህንን መሰረት አድርገው አንዳንድ ሊቃውንት ሶዶ የሚለው ስያሜ ለአካባቢው የተሰጠው የጉራጌም ሆነ የኦሮሞ ህዝቦች ወደ አካባቢው ከመምጣታቸው በፊት ሊሆን ይችላል የሚል ድምዳሜ ላይ ይደርሳሉ፡፡
ይሁን እንጂ ሶዶ የሚለው ወይም ተመሳሳይነት ያላቸው ስያሜዎችን በሲዳማ አካባቢ ማግኘት ይቻላል፡፡ ወላይታ ሶዶና ሶዶ በሎቄን ለምሳሌነት ማንሳት ይቻላል፡፡ ፈረንሳዊው አንፍሬ (1982) በሲዳማ ቋንቋ ሶዶ ወይም ሶዲቻ ማለት የቆመ ድንጋይ እንደማለት እንደሆነ ፅፏል፡፡
ይህን መሰረት አድርገው ጣሊያናውያኑ ኢነሪኮ ቸሩሊና ኮንትሮሲኒ ጉራጌዎችና ኦሮሞዎች ወደ አካባቢው ከመምጣታቸው በፊት የሲዳማ ህዝቦች በአካባቢው ይኖሩ እንደነበር ጠቅሰው የጢያና አካባቢውን ትክል ድንጋዮች ያቆማቸው እነርሱ ሳይሆኑ እንደማይቀሩ አትተዋል፡፡ ሆኖም ይህ ድምዳሜ በጠንካራ መረጃ ላይ የተመሰረተና ማረጋገጫ የተገኘለት አይደለም፡፡
ዛሬ በጢያና አካባቢው ሠፍረው የሚኖሩ ህዝቦች ትክል ድንጋዮችን “ የግራኝ ድንጋይ” ሲሉ ነው የሚጠሯቸው፡፡ ይህ አፈ ታሪክ በርግጥ በመላው ኢትዮጵያ የናኘ አፈ ታሪክ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል ለትክል ድንጋዮቹ ያለው ከበሬታ በጣሙን የቀዘቀዘ ነው፡፡ አንዳንድ ፀሐፊዎች ይህንን መሠረት በማድረግ ትክል ድንጋዮቹን ያቆሟቸው ዛሬ በአካባቢው የሚኖሩ ጉራጌዎች ቅድመ አያቶች ሊሆኑ አይችሉም ሲሉ ይደመድማሉ፡፡በሐረርና ሐርመፎ አካባቢ የተካሄዱ ጥናቶች ደግሞ ለትክል ድንጋዮቹ የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች የተሸለ አክብሮት እንዳላቸው በማሳየቱ፣ ያንን መሰረት በማድረግ የጢያና አካባቢው ትክል ድንጋዮች ያቆሟቸው ኦሮሞዎች ሊሆኑ ይችላሉ በማለት አንዳንድ አጥኚዎች ይደመድማሉ፡፡ ሆኖም በጢያና አካባቢው የተካሄዱ የአርኬዎሎጂና ፓሌዎንቶሎጂ ምርምሮች ትክል ድንጋዮቹ የቆሙት ከ12 እስከ 14ተኛው ክፍለ ዘመን ባለ ጊዜ ውስጥ እንደሆነ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡ በዚያን ወቅት የኦሮሞ ህዝቦች ወደ መካከለኛው ኢትዮጵያ መጥተው የሠፈሩ ስለመሆናቸው ማረጋገጫ ስለሌለ ድምዳሜው የሚያስኬድ አይመስልም፡፡
በአሁኑ ወቅት በአካባቢው በብዛት የሚኖሩት ጉራጌዎች ተከሏቸው ብሎ ሙሉ በሙሉ ለመናገር ባያስደደፍርም አንዳንድ ምንጮች ወደነርሱ ያመለክታሉ፡፡ የታሪክና የሥነ ቋንቋ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ከሆነ የደቡብ ሴም ቋንቋ ከሰሜን የሴም ቋንቋዎች ተለይቶ የወጣው ከክርስቶስ ልደት በፊት ከ300 ዓ.ዓ እስከ 100 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስትጥ ነው(ታደሰ ታምራት 1977)፡፡ ይህ ማለት ጉራጌዎች ከ14ኛው ክፍለ ዘመን በፊት በሶዶና አካባቢው ሰፍረው ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ ይሰጣል፡፡ ነገር ግን ጉራጌዎች በ14ኛው ክፍለ ዘመን የክርስትና እምነት፣ እንዲሁም በ16ኛው ክፍለ ዘመን የእስልምና እምነትን ተቀብለዋል፡፡ ከማዕከላዊ መንግስት ጋር በነበራቸውም ቀረቤታና በተቀበሏቸው እምነቶች የተነሳ የትክል ድንጋዮችን ታሪክ ዘንግተውት ወይም ከዘመን ብዛት ለድንጋዮቹ ይሰጡ የነበሩትን ክብር ቀንሰው ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ግን የጢያና አካባቢውን ትክል ድንጋዮች ያቆሟቸው ማህበረሰቦችን ማንነት በትክክል ለማመልከት ተጨማሪ ጥናቶች በጥልቀት መከናወን ይገባቸዋል፡፡ (ኃይሉ ዘለቀ፣1998)
